Image

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ

Benishangul Gumuz Regional State Health Bureau

በቤንሻንጉል ጉሙዝ 13 የኮሮና ቫይረስ ለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማዕከላት ተዘጋጁ

(አሶሳ፤ ሚያዚያ 02/2012) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 13 የለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማእከላት መዘጋጀታቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ፡፡ የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ እንደገለፁት በክልሉ አሶሳ ከተማን ጨምሮ በሶስት ዞኖች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል 13 የለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማዕከላት ተዘጋጅቷል። ማዕከላቱ የተዘጋጁት ቫይረሱ ቢከሰት የከፋ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ የመንግስት ጤና ጣቢያዎችና ጤና ኮሌጆችን ጨምሮ በድጋፍ የተገኙ የግል ክሊኒኮችና ሆቴሎች አስፈላጊው ቁሳቁስ እንዲሟላላቸውና ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆኑ ተደርጓል ነው ያሉት። የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ክሊኒክን ጨምሮ በጊቢው የሚገኙትን አምስት የተማሪዎች ማደሪያ ህንጻዎች ለመከላከሉ ሥራ ማስረከቡን ጠቁመዋል፡፡ በማዕከላቱ ከሶስት ሺህ በላይ አልጋዎች እንደተዘጋጁ የገለጹት ወይዘሮ ፍሬሕይወት የጤና ባለሙያዎች ስልጠና በመውሰድ ላይ መሆናቸውን ገልፀው፤ በየደረጃው ከሚገኙ አመራሮችና ጤና ሚኒስቴር ጋር የመረጃ ልውውጥ እየተደረገ ነው ብለዋል ፡፡ 26 የሰውነት ሙቀት መለኪያ መሳሪያዎችን በማሰራጨት በአሶሳ አውሮፕላን ማረፊያ፣ በሆስፒታሎችና ወደ ክልሉ የሚገቡ የህብረሰተብ ክፍሎች የሰውነት ሙቀት ምርመራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡ በክልሉ በደም ናሙና የሚደረግ የኮሮና ቫይረስ የላብራቶሪ ምርመራ ለማስጀመር ቢሮው ከጤና ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በየወረዳ ከተሞችና ቀበሌዎች ፈጣን ምላሽ የሚሰጡ ግብረሃይሎች ከጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች ጋር በመቀናጀት ቤት ለቤት የሚደረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ የማዕከላቱን አቅም በቁሳቁስና በአስፈላጊ ግብዓቶች ማጠናከር የመከላከል ሥራው ዋነኛ ትኩረት ነው ብለዋል። “አሁንም ህብረተሰቡ ማሕበራዊ ርቀቱን አለመጠበቅ እና ሌሎች መዘናጋቶች እየታዩበት ነው” ያሉት ወይዘሮ ፍሬሕይወት ህብረተሰቡ ቤት ከመቀመጥ ጀምሮ አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ የመከላከል ስራውን እንዲያግዝ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ የጤና ጣቢያው ባለሙያዎች የወሰዱትን ስልጠና ተግባራዊ ለማድረግ በየጊዜው ልምምድ እያደረጉ መሆኑን የገለጹት የአሶሳ ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ቢኒያም ቡልቱ፤ ጤና ጣቢያው ወደ ለይቶ ማቆያ በመቀየሩ የጤና ባለሙያዎቹ በስልጠናው ካገኙት እውቀት በተጨማሪ የስነ-ልቦና ዝግጅት አድርገው ወደ ሥራ መግባታቸውን አስረድተዋል። ህብረተሰቡ መጨባበጥን ጨምሮ አካላዊ ንክኪዎችን በማስቀረትና በተለይ የእጅ ንጽህናቸውን በመጠበቅ የበሽታውን ስርጭት እንዲከላከል ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በተሰጣቸው ስልጠና መሰረት በሙያቸው በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹ የጤና ባለሙያ ሲስተር ፀጋነሽ ዲባባ ህብረተሰቡ ርቀቱን በመጠበቅና እጁን ደጋግሞ በመታጠብ ቫይረሱን በመከላከል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ መልእክት አስተላልፈዋል።