Image

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ

Benishangul Gumuz Regional State Health Bureau

በክልሉ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ወደ ለይቶ ማቆያ የሚገቡ 4 ሺህ ሰዎችን ተቀብሎ ማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

(አሶሳ፣ ሚያዚያ 13/2012) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኘ ምክንያት ወደ ለይቶ ማቆያ የሚገቡ 4 ሺህ ሰዎችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት ማድረጉን የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው እየተደረገ ያለው ዝግጅት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ባለሙያዎች በተገኙበት ተጎብኝቷል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኃይማኖት ዲሳሳ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው በክልሉ በቫይረሱ ምክንያት የሚጠረጠሩ፣ ከተለያዩ ስጋት ካለቸው አካባቢ መጥተው ወደ ለይቶ ማቆያ የሚገቡ እና ከገቡ በኋላ ቫይረሱ ቢገኝባቸው የሚታከሙ 4 ሺህ ሰዎችን ለማስተናገድ ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ከተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ የሚመጡ 3 ሺህ ሰዎችን፣ በቫይረሱ የሚጠረጠሩ 500 ሰዎችን እና ከምርመራ በኋላ ቫይረሱ የሚገኝባቸው 500 ሰዎችን ከአልጋ፣ ከምግብ፣ ከባለሙያ ትብብር አገልግሎቶች ጋር ለማስተናገድ ከወዲሁ አስፈላጊው ዝግጅት ስለመደረጉም አስታውቀዋል፡፡
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ከዚህ ቀደም 260 ሊትር ሳኒታይዘር በዩኒቨርሲቲው ተመርቶ መሠራጨቱን የገለጹት ዶ/ር ኃይማኖት፣ ተጨማሪ የማምረት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም፣ ወደ ህብረተሰቡ የሚደርስ 40 ከእጅ ንክኪ ነጻ የሆነ የእጅ መታጠቢያ መሳሪያ ተመርቶ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን ጠቁመው፣ 10 የሙቀት መለያ መሳሪያ በዩኒቨርሲቲው እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
በክልሉ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እየተደረገ ያለውን ጥረት በመከታተል ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት፣ በመከላከሉ ረገድ በክልሉ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች መልካም ቢሆኑም፣ በህብረተቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋት ግን አሳሳቢ መሆኑን አመልክቷል፡፡
በኢንስቲቲዩቱ የማህበረሰብ ጤና ተመራማሪ የሆኑት አቶ የሻምበል ወርቁ፣ በክልሉ ያለው የመከላከል ሥራ ጥሩ መሆኑን ገልጸው፣ እየተሠጡ ያሉ ምክረ-ሀሳቦችን በመተግበር ረገድ ያለውን ውስንነት ለመፍታት ተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
እንደሀገር የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያ እጥረት በመኖሩ ለሁሉም አካባቢዎች በበቂ ሁኔታ ማድረስ እንዳልተቻለም ነው አቶ የሻምበል ያስታወቁት፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሳሪያው በቀዳሚነት ከሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች አንዱ ቢሆንም፣ በአቅራቢ ድርጅቶች በኩል መሳሪያውን በተፈለገው ፍጥነት ማግኘት እንዳልተቻለ ጠቁመው፣ ኢንስቲቲዩቱ መሳሪያውን ለማዳረስ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡
በሀገር ደረጃ የሳንባ ምችና መሰል ከባድ የመተንፈሻ አካል ችግር ያለባቸው ሁሉም ሰዎች እንዲመረመሩ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ መሆኑንም ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በበኩላቸው፣ ክልሉን ከሱዳ ጋር የሚያገናኘው ድንበር ቢዘጋም፣ ሰዎች በህገ-ወጥ መንገድ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ አስካሁን አለመቆሙን ገልጸዋል፡፡
መሠል እንቅስቃሴዎች ለቫይረሱ ስርጭት አደጋ በመሆናቸው፣ የክልሉ መንግስት በዚህ መልኩ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ለ14 ቀናት በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ገብተው እንዲቆዩ ማድረግ መጀመሩንም የጽ/ቤት ኃላፊው ተናግረዋል፡፡