Image

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጤና ቢሮ

Benishangul Gumuz Regional State Health Bureau

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የመደበኛ ታካሚዎች ቁጥር መቀነሱ ተገለጸ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመደበኛ ህክምና አገልግሎት ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ አሳሳቢ እንደሆነበት የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ፡፡

የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ ለኢዜአ እንደተናገሩት በክልሉ የሚገኙ ጤና ተቋማት መደበኛ የህክምና አገልግሎት መስጠታቸውን ቀጥለዋል፡፡

ሆኖም ካለፈው አንድ ወር ወዲህ ወደ ጤና ተቋማት ለመደበኛ ህክምና የሚመጡ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል።

በተለይም ለቅድመ ወሊድ፣ ለወሊድ እና ድህረ ወሊድ የሚመጡ ነፍሰ ጡር እናቶች ክትትልን ጨምሮ ለክትባት የሚመጡ ህጻናት ቁጥር መቀነስ ሁኔታውን አሳሳቢ እንዳደረገው ነው የገለጹት።

ለዚህም ምክንያቱ ህብረተሰቡ በተሳሳተ መልኩ የኮሮና ቫይረስ ታማሚዎች በጤና ተቋማት እንደሚገኙ በተሳሰተ መልክ መረዳታቸውና ቫይረሱ ይተላለፍብናል የሚል ስጋት ማሳደራቸው ሊሆን ይችላል ብለዋል።

በክልሉ የኮሮና ቫይረስ የተገኘበት ሰው እንደሌለ ያስታወቁት ኃላፊዋ፤ ይህም ሆኖ ግን ቫይረሱን አስቀድሞ ለመከላከል ከመደበኛ የህክምና አገልግሎት ውጪ በጤና ባለሙያዎች የተደራጁ 13 የለይቶ ማቆያ ማእከላት መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ክረምት መቃረቡን ተከትሎ በክልሉ ወባ በወረርሽኝ መልክ ሊከሰት የሚችልበት አዝማሚያ እየታየ መሆኑንም ሃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ ማንኛውም የህመም ምልክት ሲያጋጥመው ወደ ጤና ተቋማት በመምጣት ተገቢውን የህክምና አገልግሎት በመከታተል እራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል ።

በተለይ ክትትልና ምርመራቸውን ያቋረጡ ነፍሰጡር እናቶችና ህፃናት ወደ ጤና ተቋማት በመሔድ አገልግሎቱን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል ።

ቢሮው የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድቶ በየደረጃው የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና ኃላፊዎች የቅርብ ክትትልና እገዛ እንዲያደርጉ መመደቡን አስረድተዋል ።

በክልሉ አራት የመጀመሪያና አጠቃላይ ሆስፒታሎች፣ 46 ጤና ጣቢያዎችና 406 ጤና ኬላዎች ለአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ህዝብ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ ተብሏል።

ኢዜአ